የጦራ ከተማ አስተዳደር የክረምት በጎ ፍቃድ አብይ ኮሚቴ፤ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ ተግባራት አፈጻጸም ሪፖርትን ገመገመ፡፡
ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም. ጦራ ኮሙዩኒኬሽን
በስልጤ ዞን የጦራ ከተማ አስተዳደር የክረምት በጎ ፈቃድ አብይ ኮሚቴ፣ በ2018 ዓ.ም. የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዝግጅትና የተግባር ምዕራፍ አፈጻጸምን በስፋት ገምግሞ፣ የተጀመሩ ልማታዊና ማኅበራዊ ሥራዎች በተጠናከረ አፈጻጸም እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በግምገማው ከተለያዩ የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ጋር በመሆን በእስካሁኑ የተከናወኑ የዝግጅትና የተግባር ምዕራፍ ሥራዎች በዝርዝር ቀርበው ተገምግመዋል።
በሂደቱም የተመዘገቡ ውጤቶች በአዎንታዊ መልኩ የተገመገሙ ሲሆን፣ የሚሻሻሉ ጉዳዮች በፍጥነት እንዲስተካከሉ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
በመድረኩ እንደተገለጸው፣ የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ በ16 የተለያዩ የሥራ ዘርፎች በተቀናጀ አኳኋን እየተፈጸመ ሲሆን፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ጥገና፣ የደም ልገሳ፣ ለሴቶች፣ ለህጻናትና አቅም የሌላቸው ዜጎች ድጋፍ፣ ነፃ የጤና ምርመራ፣ የከተማ ጽዳት ሥራዎች በጥሩ አፈጻጸም መከናወናቸው ተጠቁሟል።
ይህም በጎነትን፣ አብሮነትንና የማኅበረሰብ ተሳትፎን በማጠናከር ዘላቂ የልማት ውጤቶችን ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ያሳያል።
አብይ ኮሚቴው የተግባራቱን አፈጻጸም በየጊዜው በመገምገም እንደሚመራ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ዙር ግምገማም ጠንካራ አፈጻጸሞች ይበልጥ እንዲጠናከሩ፣ የተጀመሩ ልማታዊና ማኅበራዊ ሥራዎች ፍጥነታቸውንና ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ፣ የሕዝብ ተሳትፎም ይበልጥ ተጠናክሮ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አጽንኦት ተሰጥቷል።
የግምገማ መድረኩ በጦራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ካሚል አማን የተመራ ሲሆን፣ የከተማው ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ደኑር ኮሪ፣ አስተባባሪ አካላትና የተለያዩ የከተማው አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል።
የጦራ ከተማ አስተዳደር በ2018 ዓ.ም. የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴን በተቀናጀ አመራር፣ በተቋማት ቅንጅትና በሕዝብ ንቁ ተሳትፎ በማስፈጸም፣ የማኅበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል፣ የመረዳዳት ባህልን ለማጎልበትና የልማት ውጤቶችን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጿል ።